Wednesday, 24 April 2019 | Login

Follow us on Facebook

Prophet Jeremiah Husen

ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን እንደ ግል አዳኜ አድርጌ የተቀበልኩት ማንም መስክሮልኝ አይደለም ጌታ እራሱ ነው የተገናኘኝ፡፡ ጌታን ከማወቄ በፊት በእኔ ውስጥ ብዙ የጨለማው ባህሪያት ይገለጡ ነበር፡- እሰርቃለሁ ፣ እቅማለሁ ፣ አጨሳለሁ ሁሉንም ነገር አደርግ ነበር፡፡ ከቤተሰቤ ወርቅ እሰርቃለሁ ከመኪና ውስጥ ነዳጅ እያወጣሁ እሸጣለሁ፡፡ ይህንን ባህሪዬን ለማርካት ብዙ ገንዘብ አስፈለገኝ፡፡ ስለዚህም ሳውዲ አረብያ ሄጄ ለምን ጠቀም ያለ ገንዘብ ሰርቼ ፍላጎቴን አላረካም ብዬ ወደ ሳውዲ ለመሄድ ወሰንኩ፡፡ ከጓደኞቼ ጋር ሆነን ፎርጅድ የሚሰራበት ቦታ ሄደን ለእኔ ‹‹ካሊድ ሁሴን አብድርቃድር›› በሚል ስም ፎርጅድ ፓስፖርትና መታወቂያ አሰራሁ ፡፡ ከዚያም ወደ ሳውዲ ሄድኩ ፡ ፡ እዚያ ከሄድን በኋላ የምንሰራው ዘረፋ ነበር፡፡

 

የእኔ ስራ ከሰው እጅ ሞባይልና ካንገት ላይ የአንገት ሃብል በጥሶ መሮጥ ነበር፡፡ ይሀንን ስራ እየሰራሁ በሳውድ አረቢያ ሻራሞኮሮና የተባለች ቦታ ላይ እኖር ነበር፡፡ ዝርፊያውም ብዙም አልተሳካልኝም ሌሎች ጓደኞቼ ጥሩ ጥሩ ነገር ሲዘርፉ እኔ ግን አይሳካልኝም ነበር፡፡ ሞባይል እንኳን ስቀማ የማገኘው የማይረባ ሞባይል ነበር፡፡ በዚህ ሁኔታ እያለሁ አዲስ አበባ ያለችው ያሳደገችኝ የምወዳት አያቴ ሞተች የሚባል ዜና ሰማሁ፡፡ መሄድ ስለነበረብኝ አንድ ትልቅ የመጨረሻ ዝርፊያ ለማድረግ ከጓደኞቼ ጋር ተመካከርን፡፡ የዝርፊያው እቅድ የአንድ ንጉሳዊ ቤተሰብን ሰው ቤት ለመዝረፍ ነበር፡፡ ‹‹ያንን ከማድረጋችን በፊት ግን ለመጨረሻ ምሽት ለምን ሰክረን አንደሰትም›› ተባባልንና ሰክረን ለመደሰት ወደ አበሾች መንደር ሄድን፡፡ እዚያም ጠጣን፣ ጨፈርን፣ ሐሽሽ አጨስን ሰከርን፡፡ እኩለሌሊት ሲሆን ወጥተን ሄድን ፡፡ በእጄ ሐሽሽና መጠጥ ይዤ አስፓልት መሃል እየተንገዳገድኩ ሳለሁ ፓሊሶች በመኪና አባረው በበር ገጭተው ጥለው ከነመጠጤና ሐሺሼ ያዙኝ ፡፡ ከዚያም ወደ እስር ቤት ከተቱኝ፡፡ የተያዝኩት ዝርፊያውን ሳልዘርፍ ነው፡ ፡ ተሳክቶልኝ ስዘርፍ ብያዝ ኖሮ በሳውዲ ህግ ወይ እገደላለሁ ወይም እጄ ይቆረጥ ነበር፡፡ እግዚአብሔር ግን አዳነኝ፡፡

 

ከሁለት ቀን በኋላ ወደ አገሬ አሳፍረው ላኩኝ፡፡ ወደ ሃገሬ ከመጣሁ በኋላ ግን ያለማቋረጥ 2 አመት አበድኩ፡፡ ያበድክበት ምክንያቱ በገንዘብ የምትረዳኝ የሃረር ልጅ ጓደኛ ነበረችኝ፡ ፡ እናቷ ከልጇ እንድለይ ስለፈለገች መድሃኒት አሰርታብኝ ነው እንደዚያ የሆንኩት፡፡ እብደቴ ከቤት መውጣትና ከሃገር ሃገር መዞር ነበር፡፡ የማደርገውን ነገር አላውቅም የማውቀው ነገር ቢኖር እንደህልም ሆኖ ነው ሁሉም ነገር የሚታወቀኝ፡፡ እና ከአዲስ አበባ እስከ ሐረር እሄዳለሁ ሀረር ላይ ካራማራ ጫት የሚሸጥበት አካባቢ ላይ ስደርስ ግን ራሴን አውቃለሁ፡፡ ያ እስከሚሆን ድረስ ግን እንዴት እዚያ እንደመጣሁ አላውቅም ነበር፡፡ ኤርፖርት የምቀበላቸው ሰዎች ነበሩ፡፡ ማንነታቸውን አላውቅም ግን በመናፍስቱ አለም ውስጥ ያሉ ሰዎች እንደሆኑ ነው አሁን የምገምተው፡ ፡ ከዛ መፍትሄ ቢገኝ ብለው የቤላው ንጉስ የሚባል ውቃቢ ቤት ወሰዱኝ፡፡ እዚያ ስገባ ግን ከመፍትሄ ይልቅ ችግሩ የበለጠ የሚብስበት ነገር ሆነብኝ፡፡ ለመፍትሔ ብሎ ጠንቋዩ የሆነ በጫት የተቦካ ነገር ሰጠኝ፡፡ ያ የተሰጠኝ ነገር መፍትሄ የሚሰጥ ሳይሆን ለጠንቋዩ ባሪያ የሚያደርግ ነበር፡፡ ወደ አዲስ አበባ እመጣና ሞባይልና ገንዘብ እዘርፍና የሚሸጠውን እቃ ሸጬ ሰንደል ፤ ከርቤ እጣን፤ ገለምሶ ጫትና የቀረውን ገንዘብ ይዤ እየሄድኩ እሰጠውና ተመልሼ ያንኑ ነገር አደርጋለሁ እዘርፋለሁ እሸጣለሁ እገብራለሁ፡፡ ለራሴ ግን ከገንዘቡ ምንም አልጠቀምም ነበር፡፡ ከዚህ የተነሳ እጅግ ተጎሳቆልኩ፣ የምቀይረውም ልብስ ስላልነበረኝ ልብሴ በላዬ ላይ በተባይ ተላ፡፡ የማድርበት አልነበረኝም፡ ፡ አዲሰ አበባ ስመጣ አሜሪካን ግቢ ጫማዬን ትራስ አድርጌ ነበር የምተኛው፡፡ በዚህ አይነት ህይወት ለ2 ዓመት ቆየሁና መናፍስቶች ሰኔ 2 ሊገሉኝ ሲነጋገሩ ሰማሁኝ፡፡ ተስፋ ቆረጥኩ ህይወቴ አስጠላኝ የማደርገው ግራ ገባኝ፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያለሁ ከዚያ በፊት ስለ ሐይማኖት ግንዛቤው ብዙም ስለሌለኝ ግድ የለኝም ነበር፡፡

 

ብቻ እግዚአብሔር እንዳለ አውቅ ነበር፡፡ ስለዚህም መፍትሔ እርሱ ብቻ ነው ሊሆነኝ የሚችለው ብዬ አሰብኩና ላናግረው ወደ አብዮት አደባባይ ሄድኩ፡፡ ማሃል አብዮት አደባባይ ላይ በግልጥ እንዲያየኝ ቆምኩና ወደ ሰማይ አንጋጥጬ ‹‹አታየኝም? አትረዳኝም? ›› እያልኩ ጮህኩ፡፡ ከፀለይኩ በኋላ አስጢፋኖስ ገብቼ ዛፍ ስር ቁጭ ብዬ ሳለ እንቅልፍ ወሰደኝ፡፡ ከእንቅልፌ ስነቃ ሰዓቱ 5፡30 ነው፡፡ ሰውነቴ ጭቃ በጭቃ ሆኗል፡፡ ኪሴ ውስጥ ስገባ 20 ብር አገኘሁ፡፡ ቤርጎ ለመያዝ ካሳንቺስ ሄድኩኝና አንድ መንደር ውስጥ ያለ ሆቴል ሄጄ ስጠይቅ 25 ብር ነው አሉኝ፡፡ 5 ብር ይጎለኝ ነበር በዚህ ላይ መታወቂያ የለኝም ልብሴ ያደፈ ስለነበረ ‹‹እንቢ አናከራይህም›› አሉኝ፡፡ በኋላም አንዲት ፖሊስ ረድታኝ በእርሷ ግፊት እንዳድር ተፈቀደልኝ፡፡ ሰይጣን ሊገለኝ ያቀደው ሰኔ 2 ቀን ነው፡፡ እኔ እዚያ ሆቴል ውስጥ የነበርኩት ሰኔ 1 ከሌሊቱ 7 ሰዓት ላይ ነው፡፡ ሰይጣን እቅዱን ለማሳካት እራሴን እንድገድል የሚገፋፋ ነገር አመጣብኝ፡፡ ለድምጹ ታዝዤ ወንበር ላይ ቆሜ እራሴን ለማጥፋት ኤሌክትሪክ ለመያዝ ብል ቁመቴ አልደርስም አለኝ፡፡ ከዚያ በኋላ ከኤሌክትሪክ ቦክስ ውስጥ እባብ ፤ጊንጥ ፤ዘንዶ እየወጡ በላዬ ላይ ሲወጡብኝ አየሁ፡፡ ከየአካባቢው እየወጡ ሲያስጨንቁኝ እየጮህኩ ከቤቱ ወጥቼ እየሮጥኩ ሄድኩ፡፡ ከቤት ስወጣ ደግሞ ከሰማይ የደም ዝናብ ይዘንብ ነበር፡፡ ዝናቡም ሲነካኝ በጣም ጮህኩ፡፡ እሮጥኩ ወዴት እንደምሮጥ አላውቅም በመጨረሻ ወደኩ፡፡ ወድቄም ሳለ ከሰማይ የወርቅ የሚመስል አንድ ቀበቶ መጥቶ ወገቤ ላይ ገባልኝ፡፡ ከዚያ በኋላ ከዚህ ከማየው አለም ነቃሁ፡፡ በሆቴሉ አቅራቢያ በሚገኘው የካሳንቺሱ ፅዮን ቤተክርስቲያን ውስጥ ከሌሊቱ 6፤30 ቤት ውስጥ እራሴን አገኘሁ፡፡ ዘበኛውም እንዴት እንደገባሁ አያውቅም እኔም እንዴት እንደገባሁ አላውቅም፡፡ ሰይጣን ሰኔ 2 ሳይገለኝ እግዚአብሔር ተአምራት ሰርቶ አዳነኝ፡፡ ዘበኛውን እባክህ የሚረዳኝ ሰው ካለ ደውልና አገናኘኝ አልኩት፡ ፡ ዘበኛውም ከቤተክርስቲኗ ዋና ፓስተር ጋር ደውሎ አገናኘኝና ያጋጠመኝን ሁሉ ለፓስተሩ ነገርኩት፡፡ በጣም ፈርቻለሁ እባክህን ስለው ‹‹ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን ተቀበል›› አለኝ፡፡ የኢየሱስን ስም ሲናገር በድምፁ ውስጥ የነጎድጓድ ድምፅ ሰማሁ፡ ፡

 

ከዚያም ‹‹ወደቤርጎህ ተመለስና ጠዋት እንነጋገራለን›› አለኝ፡፡ ወደ ቤርጎ ተመልሼ ገብቼ ተኛሁ፤ ተኝቼ ግን እንቅልፍ ሊወስደኝ አልቻለም፡፡ ወደቤቱ አንድ አቅጣጫ ዞር ስል አንዲት የፍየል ቅርጽ ያላት ቀንድ ያላት ሴት አየሁ፡፡ ሴትየዋ ጌታ በትር ይዞ በጎቹን የሚጠብቅበትን ስዕል ዘቅዝቃ ይዛ እየሳቀች ‹‹ማነው ከእጄ የሚያወጣህ !? ›› ትላለች፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያለን አንድ እጁ መዳፍ ላይ ‹‹እኔ ከአንተ ጋር ነኝና ክፉን አትፍራ›› የሚል በወርቅ የተቀረፀ ጽሁፍ ያለው እጅ ከሰማይ እየተምዘገዘገ መጣ፡፡ ልክ እጁ ሲመጣ እሷንም ዘቅዝቃ የያዘችውን መስታወቱንም ልክ በቦንብ እንደሚበተን ብትንትን አድርጎ አጠፋቸው፡፡ ልክ ስነቃ ቤቱ በጉም ተሞልቶ አጠገቤ ጠፍር ያደረገ እግሩ ያማረ ሰው አየሁ፡፡ እርሱም እንደዚሀ አለኝ ‹‹አንተ የእኔ ነህ ፣ በአንተ ስሜን አከብራለሁ!›› አለኝ፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ከጌታ ጋር ተገናኘሁ፡ ፡ ሌላ የሚያስገርም ነገር ሆነ ፡፡ ወደ አልቤርጎ ስገባ ልብሴ ያደፈና በጭቃ የቆሸሸ ነበር፡፡ ቤቱ ውስጥ ያለውን ቁምሳጥን ስከፍት አዲስ ከሱፍ የተሰራ ብልጭልጭ ሙሉ ልብስ ከነጫማው አገኘሁ፡፡ እስከዛሬ ያ እንዴት እንደሆነ ሳስበው ይገርመኛል፡፡ በበነጋታው ወደ ፅዮን ቤተክርስቲያን ሄድኩ፡፡ ፓስተር አብርሃምን አገኘሁት ጌታን ተቀበልኩና ማረፊያ ቤት እስከጊዜው ድረስ ሰጠኝ፡፡ ጥሩ ሞዴል የሆነልኝ ፓስተር ነው፡፡ እዚያ ደህንነት ተማርኩ፡፡ ከዚያ ወጥቼ ክብር ደመና ቤተክርስቲያን ሄጄ እዚያ ስላልገባኝ በድጋሚ ደህንነት ተማርኩና በአጠቃላይ 1 አመት ከዘጠኝ ወር ተምሬ ደህንነት ተምሪ ሲገባኝ ተጠመኩ፡፡ ስጠመቅ መንፈስ ቅዱስ ተሞላሁ ከዛን ጊዜ ጀምሮ ማንነቴ ተቀየረ፡፡ የእግዚአብሔርን መንፈስ መጠማት ጀመርኩ፡፡ እግዚአብሔር እንዲቀባኝ ለረጅም ጊዜ ፆምና ፀሎት ይዤ የጌታን ፊት መፈለግ ጀመርኩ፡፡ ከዚያ የእግዚአብሔር ድምፅ መስማት ጀመርኩኝ፡፡ ኤፍ ቢ አይ ቤተክርስቲያን መጠነኛ አገልግሎት ጀመርኩ፡፡ የእግዚአብሔር ነገር በህይወቴ ይገለጥ ጀመር፡፡ ለሰዎች እጸልያለሁ ሰዎችም ይፈወሱ ነበር፡፡

Donate Online

Thank you for your donation.Do your part

Bank : Berhan Int. Bank
Branch : Bole Branch
City : ADDIS ABEBA
State : Ethiopia
Account : 2600010003122
Swift Code : BERHETAA

Call us on these numbers

  • +251 944 72 30 90
  • +251 944 72 30 91
  • +251 944 72 30 92
  • +251 944 72 30 93

 

News Letter

Subscribe our Email News Letter to get Instant Update at anytime